Sunday, April 29, 2012

አገር በምን ይፈርሳል?----ተመስገን ደሳለኝ




 በእርግጥም ይህ ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ እንድንነጋገር የምንገደድበት ነው። ጉዳዩ የግራ-ዘመሞች ወይም የቀኝ መንገደኞች ፖለቲካ አይደለም። ጉዳዩ ኢህአዴግን የመጥላት ወይም የመውደድ አይደለም። ጉዳዩ መለስ ስልጣናቸውን ይለቃሉ ወይስ አይለቁም የሚል አይደለም። ጉዳዩ የገዥው ፓርቲ ወይም የተቃዋሚዎችም አይደለም… የሀገር ጉዳይ እንጂ። ስለዚህም የፖለቲካ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ስለሀገራችን መፃኢ ዕድል በግልፅ ተነጋግረንበት፣ ተወያይተንበት ማሰሪያ ካላበጀንለት ድንገት ከእጃችን ወጥቶ የፈሰሰ ውሃ… ሊሆን ይችላል። እናም ከድንገቴው ቀን በፊት እንወያየበት፡፡
አዎን! በኢህአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አሊያም በመድረኩ ሌበራል ወይም ሶሻል ዴሞክራሲ መቻቻል እና መደራደር ይቻላል። ከፀሀይ በታች ምንም አይነት ድርድር የማይኖረው በሀገር ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ከተስማማን ቀጣዩ ጥያቄ ሀገር ማለትስ ምን ማለት ነው? የሚል ይሆናል ማለት ነው። በእርግጥ ሀገር ማለት ፖለቲካ አይደለም። ስልጣንም አይደለም። ስርዓትም አይደለም። መንግስትም አይደለም። ኢህአዴግ ማለትም አይደለም፤ መድረክና የመሳሰሉት ተቃዋሚዎችም እንደማለት አይደለም። …እነዚህ ሁሉ ‹‹ከሀገር በእጃችን›› ፍልስፍና በኋላ የሚመጡ ጥቅማጥቅሞች ወይም ጥያቄዎች ናቸው። ለእዚህም ነው ‹‹ሀገር›› የእነዚህ ሁሉ ማዕቀፍ ነው እያልኩ ያለሁት።
ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም በ1966 ዓ.ም. ‹‹ኢትዮጵያዊነት-ልማት በህብረት›› በሚል ርዕስ በፃፉት መጽሐፍ ላይ የሀገርን ትርጓሜ እንዲህ ይገልፁታል፡-
‹‹ አገር ማለት በአንድ አይነት ሕግና በአንድ መንግስት ጥላ ስር የሚተዳደሩ ሰዎች (ህዝብ) ባለመብት የሆኑበትና የኑሮአቸው መሰረት የሚያደርጉት በወሰን የተከለለና የማይደፈር መሬታቸውን ጨምሮ የሚገልፅ ህብረት ነው።››
ደህና! ይህንን ትንታኔ ይዘን፣ ከሀገር ስለሚገኝ ማንነት አሁንም ፕሮፍ በ1986 ዓ.ም. ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ስር ከፃፉት መጻፍ እንይ፡-
‹‹ኢትዮጵያዊነት ብዙ የተለያዩ ህብረተሰቦች የተዋሃዱበት አካል ክፍል መሆን ነው። ኢትዮጵያ ከጎሰኝነት በላይ እና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የዚህች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት የደጋው ዝናም ከቆላው ወንዝ ጋር የተዛመደበት ኃይል ነው። ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሀመድ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቶ የሚደባለቅበት እምነት ነው። ኢትዮጵያዊነት በቄጠማ ጓዝጓዝ ላይ የሚታየው መተሳሰብም መፈቃቀርም ነው። ኢትዮጵያዊነት የአስተዋይነት፣ የሚዛናዊነትና የጨዋነት ባሕርይ ነው። ኢትዮጵያዊነት ረዥምና ተጽፎ ያላለቀ ታሪክ ነው፤ ብዙ ሰዎችም የተሰዉለት ስሜት ነው…›› ይሉናል። በግሌ ከዚህ በታችም ሆነ ከዚህ በላይ በኢትዮጵያዊነታችን ላይ ትንተና ባይሰጥ እወዳለሁ። ምክንያቱም ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ይህ ‹‹ህብር›› እንጂ ብሔር ብሔረሰብ… አይደለም።
እንግዲህ ዛሬ ማዶ እና ማዶ ይዘን የምንናቆርበት ኢትዮጵያዊ ማንነታችን እና ኢትዮጵያ ሀገራችን በዚህ ቅፅር የተዋቀሩ ናቸው። ስለዚህም እውነት እውነት እላችኋለሁ ይህ ቅፅር ለየትኛውም የፖለቲካ አመለካከት ወይም ልዩነት ሲባል ሊፈርስ አይገባውም፡፡ ልዩነት ያልፋል፤ ሀገር ግን አያልፍም። እናም ‹‹አገር›› እና ‹‹ማንነት›› ብለን የተስማማንባት ‹‹ኢትዮጵያ›› ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል ብቻ ለማፍረስ መሞከሩ አደገኛ መሆኑን ከሌሎች ተሞክሮ ልንማር ይገባል። ይህ ስጋት የቁም ቅዠት አይደለም፣ ይልቁንም ከበር እየደረሰ፣ ነገር ግን ልናስተውለው ያልቻልነው ግዙፍ አደጋ ሆኖብናል። በእርግጥ ቀናነቱ ካለ አደጋውን መከላከል ይችላል። ዋናው ከቀድሞ አምባገነኖች መሪዎቻችንን የመጨረሻ ሰአት ‹‹አርቆ አሳቢነት›› መማር ነው። በተለይም ከአፄ ኃይለስላሴ እና ከኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያም።
አፄው ስልጣናቸውን በሀይል ሊነጥቁ የተነሱ ወታደሮች ግራና ቀኝ እንደብራና በወጠሯቸው ጊዜ ምን ነበር ያሉት? …‹‹ለህዝባችን የሚጠቅም ከሆነ ሁሉንም ነገር ፈቅደናል። ነገር ግን አደራ ይችን ሀገር በችኩልነት እንዳታፈርሷት›› ነው ያሉት። ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያምም መጨረሻቸው በደረስ ጊዜ በአቅራቢያቸው የነበሩትን ወታደሮች አሰባስበው የሞት የሽረት ትግል አላካሄዱም፣ ይልቁንም ‹‹ሀገርም ህዝብም ከሚጠፋ እኔ ልጥፋ›› ብለው ነው የኮበለሉት፡፡ ይህንን ነው ሀገር ከፖለቲካ ድልና ሽንፈት በላይ ነው እያልኩ ያለሁት፡፡ አፄውና ኮለኔሉ ‹‹በስልጣናችን የመጣውን ገለን እንሞታለን›› ቢሉ ኖሮ ዛሬ ሀገራችን በተለያዩ የዘውግ አንጃዎች የምትመራ ብጥቅጣቂ በሆነችም ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ባለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያ በመሬት ያለው ፖለቲካ ሀገር ሊያፈርስ የሚችል እንደሆነ በቂ ምልክቶች እየታዩ ነው። ይህን ማለቴን የፖለቲካው የሀሳብ መሀንዲስ የሆነውን ኢህአዴግን ከመጥላት እና ከመውደድ ጋር በፍፁም መገናኘት የለበትም። ስለአምባገነንነትም አይደለም እያወራሁ ያለሁት። ለአምባገነንነት፣ ለአምባገነንነትማ ከኢህአዴግ በፊት ሀገራችንን የመሩት በሙሉ አምባገነኖች ናቸው። ስለምርጫ ማጭበርበርም አይደለም። የቀድሞዎቹ ጭራሹንም ምርጫ የሚባል ፖለቲካ መኖሩን አያውቁም፡፡ እያልኩ ያለሁት እነዚህ ሁሉ ሀገር ሲኖር የሚኖሩ ናቸው ነው። ይህንን በግልፅ መነጋገር ይኖርብናል። የኒኮላስ ማኪያቬሊ ‹‹ለሉዑላኑ እውነትን መንገር አንገት ያስቀነጥሳል›› የሚለውን ሰንካላ ምክር ሰምተን በፍርሃት መታጀል የለብንም። አሊያ ደግሞ ከአንገት መቀንጠስ እና ከሀገር መቀንጠስ አንዱን መምረጥ ይኖርብናል። …እንደኔ እንደኔ ከሆነ የአንገት መቀንጠሱን መርጠን ስለሀገራችንእንነጋገር፡፡
ኢህአዴግ የሚከተለው የዘውግ ፖለቲካ አደጋ ላይ መውደቅ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ነው። ከሽግግር መንግስቱ ውስጥ ሰፋ ያለ ውክልና ይዞ የነበረው የአሁኑ ‹‹ሽብርተኛ›› የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግንባር (ኦነግ) ከኢህአዴግ ጋር የነበረውን በርካታ ልዩነት ተከትሎ ‹‹ከክልሌ ውጡ›› ወደሚል የፖለቲካ አቋም የመጋፋት አዝማሚያ ያሳይ ነበር። ይህም በርካታ ዋጋ አስከፍሏአል። በእርግጥ ለኦነግም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን መሰል ፅንፍ ላይ ይቆሙ ዘንድ መደላደል የሆነላቸው ኢህአዴግ የቆመበት የዘውግ ፖለቲካ መሆኑ አያከራክርም።
የህወሓት የርዕዮተ-ዓለም መሀንዲሶች ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም ሆነ የረዥም ዘውግ ታሪክ በተቃርኖ የሚቆም ንድፈ ሀሳብን እንደ ፖለቲካ ፕሮግራማቸው ሲወስዱት ከ90 በመቶ በላይ የሆኑት ተከታዮቻቸው (ተዋጊዎቻቸው) ጉዳዩን ለመረዳት ያላቸው አቅም ውስን በመሆኑ የትጥቅ ትግሉን በበላይነት ከመወጣት አልፈው የመንግስት ስልጣን ይዘው እስኪተገብሩት እና ችግሮች እስኪከሰቱ ድርስ የሞቱለት አላማ ይህ መሆኑን በሚገባ አልተረዱም። ስለዚህም ‹‹ሀገሬ››ን ብለው ‹‹ዱር ቤቴ›› ያሉ ታጋዮችን በጅምላ መውቀሱ በራሱ ስህተት ነው። ይህ ኃላፊነት / ተጠያቂነት/ የአመራሩ ነው ሊሆን የሚችለው። ሆኖም የዚህ ፅሁፍ አላማ አመራሩን መውቀስ አይደለም። አላማው ዛሬም ቢሆን አረፈደምና ከድጋፍና ከተቃውሞ ክልል ባሻገር ርዕዮት አለሙን በየትኛውም ወገን ያለ ካድሬ እንዲፈትሸው ግፊት ማድረግ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የሚከተለውን አይነት የፖለቲካ ፕሮግራም ተከትሎ ሀገር ያስተዳድረ ወይም አያስተዳድረ ያለ /የተሳካለትም ያልተሳካለትም/ መንግስት ለማግኘት ብትፈልጉ ደክማችሁ ትተዉታላችሁ እንጂ አታገኙም። ምክንያቱም ይህ ንድፈ ሃሳብ በሌሎች ሀገራት በታሪክም ሆነ በህይወት የለምና፡፡ ምንአልባት በሙዚየሞቻቸው ልታገኙት ትችሉ ይሆናል፤ በተቀረ... ተቀበልነውም አልተቀበልነውም በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በአለማችን በብቸኝነት ቆሞ ያለው ኢህአዴግ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም ንድፈ ሃሳቡን ራሱ ልናየው የምንችለው ያለማነፃፀሪያ ነው ማለት ነው። ልክ ‹‹የተዘጋች ቤተ መቅደስ›› ትባል እንደነበረው የኤኒቨር ሆጃ አልባኒያ።… ለነገሩ የአልባኒያ መንፈስ በዚህም ቤት ያለ ይመስለኛል። ዘውገኝነቱ ግን እዚህ ይብሳል። ጉዳቱም የከፋ ነው፡፡
ለዚህም መሰለኝ የ‹‹ዘውግ ፖለቲካ››ን ‹‹አፍራሽ›› ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች የሚተቹት። ይህ እውነት ቢሆንም አምባገነኖች ብዙውን ጊዜ አገዛዙን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ ብቻ የዘውግ ፖለቲካን እንደሚከተሉ ምሁራኖች ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ለNational security (ለሀገር ደህንነት) ፍፁም አደገኛ በመሆኑ ውሎ አድሮ ሀገር ከማፍረስ አይመለስም።
ከሀገሪቱ የረዥም ዘመን ታሪክ ዘውገኝነትን እንፈልግ ብንል በ‹‹ወንዝ›› የተከፈለ አስተዳደር የምናገኘው ምናአልባት “The Era of princes” /ዘመነ መሳፍንት/ እየተባለ በታሪካችን በሚጠቀሰው ጊዜ ነው። በዚያ ወቅት የነበረው የሀገሪቱ አስተዳደር በጎበዝ አለቃ (በራስ፣ ደጃዝማች፣ ፊታውራሪ…) ከመከፋፈሉ ውጭ በኢትዮጵያ የነበረው “Power struggle” (የስልጣን ትግል) እንጂ የ‹‹ወንዝ›› (የክልል) ፖለቲካ አልነበረም። በ‹‹ፊውዳል››ነቱ የሚወቀሰው የነገስታቱ አገዛዝ ከፈረሰ በኋላ የተተካው የደርግ ስርዓት የለየለት አምባገነን ነው። ሁሉንም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን በድብቅ ሳይሆን በይፋ ገርስሶአል። ነገር ግን ርዕዮተ አለሙ የተቀኘው በሀገር አንድነት ላይ ነው። እንዲያውም ስርዓቱ መላውን የስልጣን ዘመኑን የጨረሰው ‹‹እንገንጠል›› እና ‹‹እንከለል›› ከሚሉ ብሔርተኛ ቡድኖች ጋር ‹‹አንድ ሀገር አንድ ህዝብ›› በሚል አቋም በጦር መሳሪያ ሲፋለም ነው። ‹‹አብዮታዊ እናት ሀገር ወይም ሞት›› የሚለው መፈክርም ቢሆን የፖለቲካው ፍልስፍና መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ለመፍጠር የነበረው አስተዋፅኦ በቀላል የሚታይ አይደለም። ነገር ግን ይህ ‹‹የአንድ ሀገር አንድ ህዝብ›› ፖለቲካ በኃይል ከተሸነፈ በኋላ በዘውግ ፖለቲካ ተተክቶአል፤ መፈክሩም ከ‹‹እናት ሀገር…›› ወደ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች…›› ተቀይሯል።
በእርግጥ ይህን ንድፈ ሀሳብ እስታሊናዊ ትንታኔ የሚሰጡት ቢኖሩም፣ ከማኪያቬሊ Divided and Rule (ከፋፍለ ግዛ) ፍልስፍና ጋር የሚያቆራኙት ይልቃሉ። ይህ ፍልስፍና ለ‹‹ቅኝ አገዛዝ›› አስተዳደር ተግዳሮቶችን መሻገሪያ ይሆን ዘንድ እንግሊዝ ወደ መሬት በማውረዱ ግንባር ቀደም ነች። በቅኝ ግዛት ዘመን እንግሊዞች ይከተሉት የነበረው አስተዳደር Indirect Rule (የዘወርዋራ አስተዳደር) ሲሆን ይህንንም ለመተግበር የግድ በኃይል የያዙትን ሀገር በዘውግ ወይም በሃይማኖት ይከፋፈሉታል። እንደምሳሌ የቀድሞዋን ‹‹ሮዲዥያ›› ዛምቢያ እና ዙምባቤ ሲሉ በዘውግ የከፈሉበትን ወይም ህንድና ፓኪስታንን በሃይማኖት ከፈለው ሁለት ሀገር ያደረጉበትን ታሪክ ማየት እንችላለን።
ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ደግሞ የዘውግ አስተዳደሩ ሀገሪቱን ከአንድ ሀገር ወደ ዘጠኝ ክልሎች የሸነሸነበትን ፖለቲካ እናገኛለን። ይህ ሁኔታ በወቅቱ ብዙ የተተቸ እና ተቃውሞ የደረሰበት ቢሆንም ኢህአዴግ በበኩሉ ትችቱን ‹‹የነፍጠኛ ተቃውሞ›› እያለ ሲያጣጥለው ቆይቶአል። ሆኖም በብዙ ምሁራኖች ‹‹የከፋፍለ ግዛ እስትራቴጂ ነው›› በሚል ይቀርብ የነበረው አሳማኝ ትንተና ዛሬ ላይ ሲታይ ለእውነታው በእጅጉ የቀረበ እየሆነ ነው። አደጋው ምን ያህል እየቀረበ እንደሆነ ለማወቅ ሁለት ምሳሌዎችን ብቻ እንይ፡፡ የጋምቤላን እና የጉራፈርዳን።
እንደሚታወቀው ከ1983 ዓ.ም. በፊት የዛሬው ጋምቤላ ክልል በኢሊባቡር ክፍለ ሀገር ስር የሚገኝ አንድ የሀገሪቱ ክፍል ነው። ነዋሪዎቹም የአካባቢው ተወላጆች የሆኑትን ኑዌር፣ አኝዋክ፣ ኢታንግን… ጨምሮ በደርግ Resettlement program (የሰፈራ ፕሮግራም) ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ኢትዮጵያውያኖች ናቸው። ደርግ ሰፈራውን ሲያካሂድ እንደምክንያት የአስቀመጠው ሁለት ነገሮችን ነው። የመጀመሪያው በአካባቢው የነበረው የእርሻ ስራ ኋላ ቀር በመሆኑ አዲስ መጤዎቹ ያስተምሯቸዋል፣ የባህል ልውውጥ ይኖራል፣ ሀገራዊ አንድነት ይጠናከራል፣ ከዘውግ ይልቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ይጎለብታል የሚል ሲሆን ሁለተኛው በድርቅ የተጠቁ አካባቢ ነዋሪዎች ሰፋፊና ለም ሆና ነገር ግን ስራ ላይ ያልዋለ መሬት ወዳለበት አካባቢ የማስፈር እቅድ ድርቅን ለመከላከል ፋይዳ አለው በሚል ነው።
እንግዲህ ወደ ኢሊባቡር /ጋምቤላ/ የተካሄደው ሰፈራ ከእዚህ አንፃር ነበር። ሆኖም በ1983 የመንግስት ለውጥ ሲመጣ የርዕዮተ- ዓለም ለውጥም አብሮ መጣ። ያ ርዕዮተ-ዓለም የሚያበረታታው ደግሞ ሀገራዊነትን ሳይሆን አውራጃዊነትን ሆነ። እናም ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞና ጋምቤላ… እየተባለ በዘውግ መከለል ሲጀመር ቀድሞ የነበረው ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› ብዥታ ውስጥ ገባ። ለምሳሌ በጋምቤላ የአካባቢው ተወላጆች ከሌላ አካባቢ ከመጡት ይልቅ ንፁህ ጋምቤላዊነትን ያንፀባርቁ ጀመር፤ ከዚህም አልፎ ከአማራ አሊያም ከትግራይ የመጣው ኢትዮጵያዊ የሁለት ዕድል ተጠቃሚ ተደርጎ በጋምቤላ ተወላጆች ዘንድ ተወሰደ። ይህም ብቻ አይደለም ጋምቤላ ያልተወለደ በጋምቤላ እንደሁለተኛ ዜጋ የመታየቱ አዝማሚያ ለ‹‹መጤው›› የመጀመሪያ ዜጋ ሊሆን የሚችልበትን የተወለደበትን ክልል እንዲያልም አስገድዶታል። ይህ ደግሞ ሀገሬ የሚለው ኢትዮጵያን ሳይሆን የተወለደበትን አካባቢ እንዲሆን ገፍቶታል። ዛሬ በጋምቤላ ያለው ያለመግባባትም ኢህአዴግ እየተከተለ ካለው የዘውግ ፖለቲካ ፍልስፍና የሰረፀ እንጂ ከሰማይ እንደመብረቅ የወረደ ዱብ ዕዳ አይደለም።
ከዚህ በተቃራኒ የሚቆም ተሞክሮ እንደ ምሳሌ ማየት ካስፈለገ ደግሞ አሜሪካንን እና ጣሊያንን ማየት እንችላለን። መቼም የአሜሪካን ቀዳማይ መስራች አባቶች ታሪክ እንደሚነግረን ታላቂቷን አሜሪካ የገነቡት ተወላጆቹ ሳይሆኑ፤ መጤዎቹ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለረዥም አመት ራሳቸውን ‹‹አሜሪካዊ›› አድርገው በሚቆጥሩ ዜጎች መካከል ከፍተኛ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህን ጊዜም ነው አሜሪካኖች ‹‹ምንጊዜም አሜሪካ›› የሚለው መንፍስ ይቀድም ዘንድ በተወላጆቹ (ሬድ ኢንዲያን) እና በመጤዎቹ (አንግሎሳክሰን፣ ኤዢያ፣ አፍሪካውያን…) መካከል ልዩነት ይጠፋ ዘንድ ቀን ከለሌሊት የሰሩት፡፡ ለዚህ ፍልስፍናም በዋናነት የተጠቀሙት የሰፈራ ፕሮግራምን ነው። በእርግጥ የአሜሪካኖቹ የሰፈራ ፕሮግራም በአንድ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከቦታቸው በማስነሳት ወደሌላ ቦታ በመውሰድ አይደለም፡፡ የእነሱ የሰፈራ ፕሮግራም የተተገበረው ተቋምንና ሪሶርስን በማንቀሳቀስ የተከናወነ ነው። ለምሳሌ አንድ ግዙፍ ተቋም ከነበረበት ቦታ ተነስቶ ‹‹ተገለልን›› የሚሉ ዜጎቸ ወደሚበዙበት አካባቢ እንዲሄድ ይደረጋል። ይህንንም ተከትሎ ከተቋሙ ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ ሰዎች አብረው ይሄዳሉ። በዚህም የባህል እና የልምድ ልውውጥ ያደርጋሉ። ይህ ሁኔታም ውሎ አድሮ ልዩነታቸውን እያጠበበው አንድነታቸውን እያጠናከረው ዛሬ የደረሱበት ታሪክ ላይ አድርሶአቸዋል። በጣሊያንም ያለው ይህ ነው። የጣሊያን ትርክት እንደሚያስነብበን ደቡብ ኢጣሊያ (ሲሲሊ) እና ሰሜኑ በስልጣኔ በእጅጉ የተራራቁ ከመሆናቸውም ባሻገር አብዛኛው የሲሲሊ ተወላጅ እራሱን እንዲሲሲሊያውያን እንጂ እንደ ጣሊያናዊ አይቆጥርም። ይህ ችግርም ይቀረፍ ዘንድ መንግስት የአሜሪካኖቹን አይነት የሰፈራ ፕሮግራም በስራ ላይ እያዋለ ነው። በዚህም መሰረት የሮም መንግስት ግዙፍ ተቋማትን ከሮም ወይም ከሚላንእና ከመሳሰሉት የአደጉ ከተሞች ነቅሎ ሲሲሊ ላይ ይተከላል። ይህን ጊዜም በርካታ የተቋሙ ሰዎች አብረው ወደ ሲሲሊ ይሄዳሉ። የሲሲሊ ተወላጆችም በተቋሙ ምክንያት የስራ እድልን ጨምሮ የባህል፣ የልምድ…ልውውጥ የሚያደርጉበትን አጋጣሚ ያገኛሉ። ከዚህ ሌላ ከሲሲሊም ወደ ሰሜን ጣሊያን የሚሄዱበትን የተለያዩ ስልቶች ጣሊያን ትጠቀማለች። በዚህም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲሲሊ ተንሰራፍቶ የነበረውን የማፊያ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ሲሲሊያዊነትንም ሰባብረው ጣሊያናዊነትን እየገነቡ ነው። ይህ ሁኔታም ውሎ አድሮ ንፁህ ሲሲሊያዊ የሚል ስሜትን አዳክሞ አንድነትን ያጎለብታል።
ወደኢትዮጵያ ስንመጣ የምናገኘው የዚህን ግልባጭ ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አማራዊነት፣ ትግሬያዊነት፣ ኦሮሞአዊነት፣ ጉራጌያዊነት…፤ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈል ላይ፣ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ አውራጃዊነት ጥሰው እንዲወጡ እየተመቻቸላቸው ነው፡፡ የጉራፈርዳ ቀውስም ከዚሁ የመነጨ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እንዳሉት በጉራፈርዳ የሰፈሩት የምስራቅ ጎጃም ተወላጆች ናቸው። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ወደጉራፈርዳ እንዴት መጡ የሚለውን እንይ፡ ፡ ኢህአዴግ በሚከተለው የፖለቲካ ፍልስፍና ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ክልላዊነት ጎልቶ ወጥቶአል። ክልላዊነት ብቻም አይደለም ዞናዊነትም እንዲሁ እየጎለበተ ነው። ከዚህ ቀደም ስልጤ በዞን ደረጃ ይዋቀር ዘንድ የአካባቢው ተወላጆች ያደረጉትን የፖለቲካ ትግልና የተሳካላቸውን ተሞክሮ ማስታወስ ያስፈልጋል። እናም የጉራፈርዳ እና የምስራቅ ጎጃም ትስስር እንዲህ የጀመረ ነበር። …ከለታት በአንዱ ቀን ቤንች ማጂ ዞን ውስጥ የሚኖሩ የሚንጥ ተወላጆች ‹‹በዞን ደረጃ እንዋቀር›› ሲሉ ለክልሉ መንግስት ጥያቄ ያቀርባሉ። በወቅቱ የሚንጥ ተወላጆች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የክልሉ መንግስትም ቁጥራቸው በዞን ደረጃ ለመዋቀር የሚያስችል እንዳልሆነ ይነግራቸዋል። ይህን ጊዜም ምስራቅ ጎጃም አካባቢ ያሉ ሰዎች ወደ አካባቢያቸው መጥተው እንዲሰፍሩ እና ለም የሆነ የእርሻ መሬት እንዲወስዱ የሚንጥ ኤሊቶች ያስተባብራሉ። ከዚህ በኋላም የምስራቅ ጎጃም ነዋሪዎች ቤንች ማጂ ዞን መጡ። የሚንጥ ተወላጆችም በዞን ደረጃ የመዋቀር ጥያቄያቸውን ድጋሚ አቀረቡ። አዲስ ሰፋሪዎቹም (ከምስራቅ ጎጃም የመጡት) ተቆጥረው በዞን ደረጃ ለመዋቀር ስላስቻላቸው ‹‹ጉራፈርዳ›› የሚባል ዞን ተዋቀረ። ይህ ከሆነም ከአመታት በኋላ ነው የ‹‹ውጡልን›› ፖለቲካ የመጣው።
ይህ አይነቱ ፖለቲካ ነው ሀገር የሚያፈርሰው፡፡ ውጡልን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፓርላማ ባቀረቡት ንግግር ‹‹ውጡልን››ን የደገፉት ይመስላሉ። ልክ ምስራቅ ጎጃም ከኢትዮጵያ ውጭ ወይም አፍጋኒስታን አካባቢ ያለ ይመስል ደጋግመው በጎ ባልሆነ መንፈስ ሲያነሱት ነበር።
መቼም ይህ ጨዋታ አደገኛ መሆኑን የእድሜያቸውን አብዛኛውን ክፍል በፖለቲካ ውስጥ ላሳለፉት ጠቅላይ ሚንስትር ይጠፋቸዋል ማለት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ነገ አማራው ተነስቶ ‹‹ውጡልኝ›› ቢል ወይም ሌላው ብሔር የብሄሩ ተወላጅ ያለሆነውን ‹‹ከክልሌ ውጣልኝ›› ቢል ሊከሰት የሚችለው አደጋ የፖለቲካ ለውጥ ወይም የመንግስት ለውጥ ብቻ አምጥቶ የሚያባራ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሀገርን ነው የሚያፈርሰው፡፡ እናም እስከዛሬ ስንነታረክበት እንደነበረው ‹‹በጆንያ ውስጥ ማን የበላይ ይሁን?›› ከሚለው የፖለቲካ ቁማር በዘለለ ጆንያውን ቀዶ ለመውጣት ባንሞክር ይሻላል፡፡ የዘውግ ፖለቲካ ቀዳሚው መዘዝን ተንታኞች ‹‹አስበልጦ የመጫረት አባዜ›› /Ethnic Outbidding effect/ ሲሉ የሚጠሩት ‹‹ፖለቲካዊ ዕዳ›› ነው። የተንታኞቹ ድምዳሜ የዘውግ ፖለቲካ የአደባባዩ ብቸኛ ተዋስኦ ሲሆን የየብሔሮቹ ልሂቃን የተሻለ የፖለቲካ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ የየብሔሮቻቸውን ጥያቄዎች አጎነው እና አክርረው ያቀርቡታል። በዚህ አካሄዳቸውም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ የትኞቹም ብሔሮች እርስ በርስ የሚኖራቸውን ግንኙነት በእጅጉ ያሳሳዋል። እናም የዘውግ ፖለቲካ በበለጠ ሲፋፋ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ፖለቲከኞችም በሀገራዊ ጥያቄ ላይ አብረው ከመቆም ይልቅ በየብሔሮቻቸው ሼል ውስጥ ይቀረቀራሉ። የዚህ ተራዛሚ ተፅዕኖ ሀገራዊ የጋራ የማንነት ጥያቄን ማደብዘዝ ይሆናል እንደተንታኞች አረዳድ።
ለዚህም ነው ኢህአዴግ አምባገነን ነው፣ የለም ዴሞክራት ነው፤ ምርጫ ያጭበረብራል፣ በፍፁም ህዝቡ ነው የመረጠው፤ በሰላማዊ ትግል ይለቃል፣ አይለቅም… በመሳሰሉት የፖለቲካ ጨዋታዎች ከመቆመር በዘለለ ስልጣንን ለመጠበቅ ሲባል መከፋፈልን እና አንዱ ሌላውን ‹‹ከክልሌ ውጣ›› ሲል በማይታይ እጅ ማጨብጨብና መገፋፋቱ ፖለቲካ ሳይሆን ሀገር ማፍረስ ነው የምለው። ፖላንድ እ.ኤ.አ. በ1919ዓ.ም እስከተፈረመው የቫርሳይለስ ስምምነት ድረስ ከ200 አመት በላይ ከአለም ካርታ ላይ ጠፍታ ነበር። አርማኒያም በሌኒን ሩሲያና በከማል አታ ቱርኪ ወረራ ከምድረ ገፅ ጠፍታ እንደነበረ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። በእርግጥ ለፖላንድ እና ለአርመኒያ መጥፋት የውጭ ተፅዕኖን እንደዋነኛ ምክንያት ልናነሳው እንችል ይሆናል። ነገር ግን የዚያድባሬን ታላቂቷ ሶማሊያ ለአራት መበጣጠስ ከውጭ ተፅዕኖ ጋ በፍፁም አናገናኘውም። እናም 50 እና 60 አመት በስልጣን ለመቆየት ይህን አይነቱን የፖለቲካ ሴራ ባናሴር የተሻለ ነው። ትውልድ በትውልድ ይተካል፤ ሀገር ግን…
...ከላይ በማሳያነት የጠቀስኳቸው የጋምቤላ እና የጉራፈርዳ ሁነቶች በግሪክ ስነ- ተረት /Mythology/ ላይ የሚተረከውን የ‹‹ፓንዶራ ሳጥን›› /Pandora’s box/ ወግ ያስታውሰኛል። ሲነገራት አልሰማ ያለችው ፓንዶራ የህይወት መከራዎችን ያጨቀውን ሳጥን ገፍታ ጣለችው። ሳጥኑን በፍጥነት ወደነበረበት ለመመለስ የሞከረው አባቷ /ባሏ/ ሳጥኑን ሲዘጋ በውስጥ የቀረው ተስፋ ብቻ ነበር ይላል የግሪኩ ተረት። እናም የሰው ልጅ በተስፋ ብቻ ይኖር ዘንድ ግድ ሆነ።
የዘውግ ፖለቲካን አሁን ባለው መልክ እንዲቀጥል መፍቀድ ሀገራችንን ሊያፈራርሱ የሚችሉ የግጭት መስመሮችን ወደአደባባዩ ማምጣት እንደሆነ የሃያ ዓመቱ የፖለቲካው ጉዞ እያሳየን ነው። እነዚህ መከራዎች አንዴ ከሳጥናቸው ከወጡ በምን እንመልሳቸዋለን? እንዴትስ መልሰን ኢትዮጵያን ልናገኛት እንችላለን?

posted Apr 29, 2012 2:40 AM by Misrak Link   [ updated Apr 29, 2012 2:45 AM ]






No comments: